በቅርቡ ብዙ አዳዲስ ምርቶች ተብለው የገቡ የሳምሰንግ ስልኮችን እያየው ነበር፡፡ እንደ ውስጥ አቅማቸው ተመዝነው ከ10 ሺህ ብር በታች የሚሸጡ ስልኮችን ከ20 እስከ 25 ሺህ ብር ባለው ሬንጅ ውስጥ ለመሸጥ ገበያ ላይ ሲወጡ አይቼ ታዝቤለው፡፡ በሃገሬም ባለው የንግድ ሥርዓት የበለጠ ተስፋ አስቆርጦኛል፡፡
በተለምዶ ኢትዮጵያ ውስጥ የሚኖሩ አብዛኛዎቹ ሰዎች ስማርት የስልክ ቀፎ በሚገዙበት ጊዜ ከላይ በውበቱ ላይ እንጂ ከውስጡ ባለው አቅም ላይ ‹‹ምንም ትኩረት አይሰጡም›› ማለት ይቻላል፡፡ ይህ በዋናነት የሚከሰተው ከዕውቀት ማነስ የተነሣ ሲሆን የስልክ ቀፎው ከላይ ሲታይ ግን እጅግ ያማረ ስለሆነ ከገዙት በኋላ ሳያውቁት አላስፈላጊ ኪሳራ ውስጥ ይገባሉ ማለት ነው፡፡
ኢትዮጵያውያን ሰዎች ብዙን ጊዜ በጥልቀት የመጠየቅና የማወቅ ፍላጎት ስለሌላቸው እንዲሁም ‹‹ምናልባት የማላውቀውን ጠይቄ ብዋረድስ›› የሚል ስሜት በውስጣቸው ስለሚፈጠርባቸው ምንም በጥልቀት ሳይጠይቁ ገንዘባቸው የማይሆን ኤሌክትሮኒክስ ዕቃ ላይ ሲያፈሱ ይታያሉ፡፡ የስማርት ፎን ስልክ ሻጭ ይህንን የሰዎች ባህሪይ በሚገባ ስለሚያውቅ እንዲሁ በንግግር ብቻ የስልኩን አቅም በመንገር ያለ ምንም ማረጋገጫ እንዲሳቡ እንዲያምኑትና እንዲገዙት ያደርጋል፡፡ በቀላሉም ገንዘባቸውን ይበላቸዋል ማለት ነው፡፡
ማንኛውም ሰው የስልክ ቀፎ ከመግዛቱ በፊት ሁልጊዜ እንዚህን ጥንቃቄዎች ማድረግና የስልኩን ትክክለኛነት ማረጋገጥ አለበት፡፡ ይህን ለማድረግም ከዚህ በታች ያሉትን መንገዶች መጠቀም ይችላል፡፡
ደረጃ 1 – ቼክ ማድረጊያ ሌላ ስማርት ስልክ ማዘጋጀት፡፡
ብዙን ጊዜ ሻጮች ጋር ነጻ ዋይፋይ ስለማይኖር እንዲሁም ገዢዎች የGoogle Account ስለማይኖራቸው ተጨማሪ ቼክ ማድረጊያ ሌላ ስልክ ማዘጋጀት የግድ ይላል፡፡ አብርዎት የሄደውን ሰው ስልክ መቀጠም ይችላሉ፡፡ ይሄ የተዘጋጀው ስልክ ላይ የXender እና የCPU X – Device & System info App መጫን አለበት፡፡
ደረጃ 2 – ከሻጭ ጋር ቅድመ ጥያቄና መልስ በጥንቃቄ ማድረግ
ስልኩን በእጅዎ ከመንካትዎ በፊት የስልኩ ቀፎ በነጋዴው እጅ ላይ እያለ ለነጋዴው እነዚህን 3 ጥያቄዎች ይጠይቁት፡፡
- 1ኛ የስልክ ቀፎው አዲስ መሆኑን ፣
- 2ኛ ስልኩን ቼክ በማድረግ የውስጡን አቅም ማረጋገጥ እንደሚፈልጉ ፣
- 3ኛ ህጋዊ የቫት ደረሰኝ እንዳለው፡፡
ለእነዚህ 3 ጥያቄዎች ትክክለኛው መልሶች የሚሆኑት፡-
- 1ኛ አዎ የስልክ ቀፎው አዲስ ነው!
- 2ኛ አዎ ይፈቀዳል፡፡ ቼክ ያድርጉና የውስጡን አቅም ያረጋግጡ!
- 3ኛ አዎ! ህጋዊ የቫት ደረሰኝ አለኝ፡፡
ከእነዚህ 3 ጥያቄዎች የሻጩ መልስ አንዱን ካላሟላ ሳይገዙ ጥለውት ይሂዱ! ገንዘብዎትን ከመበላት ያድኑ!!!
ሻጩ ጥያቄዎቹን በትክክል ከመለሰ ወደሚቀጥለው ደረጃ ይቀጥሉ፡፡
ደረጃ 3 – የስልክ ቀፎው ትክክለኛ መሆኑን ለማረጋገጥ እነዚህን ቅደም ተከተል ይከተሉ፡፡
አሁን ዋና አላማችን CPU X – Device & System info የተባለውን App በመጠቀም ትክክለኛውን የአዲሱን ስልክ የውስጥ አቅም ማወቅ፡፡ ይህንን ለማድረግ፡-
- አስቀድመው የአዲሱን ስልክ Bluetooth ON ያድርጉ፡፡ Discover በሌሎች ስልኮች ለመደረግ Available መሆኑንም ቼክ ማድረግ አይዘንጉ፡፡
- አዲሱ ስልክ የXender App ስለማይኖረው አስቀድመው ባዘጋጁት ስልክ ላይ የተጫነውን የXender App ይክፈቱትና ራሱን Xender የተለውን App ወደ አዲሱ ስልክ በBluetooth ሼር ያድርጉ፡፡ ይህንን ለማድረግ፡- ራሱ Xender App ውስጥ ያለውን MENU በመጫን SHARE WITH BLUETOOTH የሚለውን ይምረጡ፡፡ አዲሱን ስልክ ሲያገኙት ወደ እርሱ ይላኩት፡፡
- አሁን አዲሱ ስልክ ላይ በBluetooth የገባውን የXender App ይጫኑት፡፡ ስለዚህ ሁለቱም ስልኮች በXender App መገናኘት ይችላሉ ማለት ነው፡፡
- በመጨረሻም ሁለቱንም ስልክ በXender App በማገናኘት CPU X – Device & System info የተባለውን App ከተዘጋጀው ስልክ ወደ አዲሱ ስልክ ይላኩትና ይጫኑት፡፡
የዚህ ሁሉ ደረጃ ዋና ዓላማው CPU X – Device & System info የተባለውን ይህንን ቼክ ማድረጊያ App በአዲሱ ስልክ ላይ መጫን ስለሆነ እርስዎ የሚመቸዎትን መንገድ መጠቀም ይችላሉ፡፡ ይህንን በXender App ማሳካት ካልቻሉ፡፡ የግድ WiFi እና የእርስዎን የጎግል አካውንት በመጠቀም እዛው አዲሱ ስልክ ላይ ከPlaystore በቀጥታ CPU X – Device & System info የተባለውን አፕ መጫን ይችላሉ፡፡
ደረጃ 4 – አሁን imei.info የሚባለውን ድረ-ገጽ በመጠቀም የስልኩን የውስጥ አቅም መረጃ ከድረ-ገጹ ላይ ካለው ጋር እናስተያያለን፡፡
ይህ imei.info የሚባለው ድረ-ገጽ የእያንዳንዱን የተመረተውን ስልክ Serial Number በዳታቤዝ የያዘ ሲሆን የእያንዳንዱንም ስልክ የውስጥ አቅም (Specification) መረጃ አብሮ ይዟል፡፡ ስለዚህ እርስዎ የሚገዙት አዲሱ ስልክ ላይ ያለውን የውስጥ አቅም መረጃ ከድረ-ገጹ ላይ ካለው ጋር ካልተመሳሰለ ስልኩ ኦሪጂናል አይደለም ማለት ነው፡፡ ይህንን ለማረጋገጥ፡-
- ቀድመው ባዘጋጁት በሌላ ስልክ ላይ imei.info የሚባው ድረ-ገጽ ላይ Chrome ብራውዘር በመጠቀም ይግቡ፡፡ አዲሱ ስልክ ላይ WiFi ካለም መጠቀም ይችላሉ፡፡
- አዲሱ ስልክ ላይ *#06# በመጫን Serial Number ያግኙ፡፡ ብዙን ጊዜ ሁለት Serial Numbers በተርታ ስለሚቀመጡ እያንዳንዱን መሞከር ይችላሉ፡፡
- የመጀመሪያውን Serial Number በimei.info ድረ-ገጽ ላይ ባለው የጽሑፍ ማስገቢያ ውስጥ ያስገቡና CHECK የሚለውን Button ይጫኑ፡፡
- ወዲያው ፈልጎ ሲጨርስ አዲሱን ስልክ በግልጽ ከነምስሉ ያዩታል፡፡ የውስጥ አቅም መረጃውም በዝርዝር ይቀመጣል፡፡ በሁለቱም Serial Numbers ተሞክሮ ስልኩ ካልተገኘ መሞከርዎን ያቁሙ፡፡ ስልኩን እንዳይገዙ፡፡
- በመቀጠል CPU X – Device & System info የተባለውን App በአዲሱ ስልክ ላይ ይክፈቱና ከimei.info ድረ-ገጽ ላይ ካለው የውስጥ አቅም መረጃ ጋር ያስተያዩ፡፡ ብዙን ጊዜ የካሜራው Mega Pixel ይጭበረበራል፡፡ RAM Memory እና Storage አቅም ላይም ትኩረት ያድርጉ፡፡ ተመሳሳይ ከሆነ ስልኩን ይግዙት፡፡ ተመሳሳይ ካልሆነ ግን ስልኩን እንዳይገዙ፡፡
ተጨማሪ መረጃ ለSAMSUNG ስማርት ስልኮች
*#0*# በመጫን እያንዳንዱን የአዲሱን ስልክ Features ቼክ ያድርጉ፡፡ በተለይ ስክሪኑን፡፡ አንድ ችግር ካገኙበት ስልኩን እንዳይገዙት፡፡
ማጠቃለያ
ይህ የጥንቃቄ መረጃ ለመተግበር በሚፈልጉበት ጊዜ ብዙን ጊዜ ሻጮች ፍላጎት ላይኖራቸው ይችላል፡፡ አንዳንዶቹ እንደውም በማታለያና በሚያሳምን ቃል በመናገር እርስዎ አዲሱን ስልክ ቼክ ሳያደርጉ እንዲወስዱ ይፈልጋሉ፡፡ እንደዚህ አይነት ነገር ካጋጠመዎት ስልኩን ጥለውት ይሂዱና ሌላ ሻጭ ይፈልጉ፡፡ ገንዘብዎትን ከመበላት ይጠብቁ!!!