በርግጥ በዚህ ባለንበት በኢንፎርሜሽን ዘመን ቴክኖሎጂው ሥራን እቤታችን ድረስ ማምጣቱን የምንዘነጋውና የምንክደው ነገር አይደለም፡፡ ለዚህ ማስረጃው ደግሞ በኢትዮጵያ ውስጥ ብዙ ሰዎች በዩቲዩብ ላይ ሥራ እየሠሩ እየተከፈላቸው መሆኑን በወሬም በተግባርም አይተናል፡፡
ሌላው የሚያስገርመው ነገር ግን አንዳንድ ገንዘብን የሚወዱ ሰዎች ገንዘብን ለማግኘት ቶሎ ካላቸው ጉጉት የተነሣ ብዙ ሰዎችን ‹‹ኦንላይን ሥራ በመሥራት በአጭር ጊዜ ሚሊየነር መሆን ትችላላቹ›› እያሉ ማታለል ጀምረዋል፡፡
በርግጥ በኦንላይን ላይ ሥራ በመሥራት በአጭር ጊዜ ሚሊየነር መሆን ይቻላል ወይ ብለን ስንጠይቅ መልሱ በአጭሩ፡- አይቻልም ነው፡፡
ለምን ካልን፡-
በአጠቃላይ የኦንላይን ሥራ ሲባል ልክ በሚዳሰሰው ዓለም ላይ እንዳለው እንደ መደበኛ ሥራ በኢንተርኔት ላይ በጥንቃቄና በስትራቴጂ የሚሰራ ሲሆን ማንም ሰው በሚዳሰሰው ዓለም ላይ በቀላሉ በአጭር ጊዜ ውስጥ ሚሊየነር መሆን እንደማይችለው ሁሉ በኦንላይን ሥራ ላይም በአጭር ጊዜም ሚሊየነር መሆን አይችልም ማለት ነው፡፡ ይህ ስለ ኦንላይን ሥራ ሲታሰብ ሁልጊዜ በጭንቅላት ውስጥ ሊያዝ የሚገባው አስተሳሰብ ሲሆን አንድ ሰው ግን በኦንላይን ላይ ሥራ በመሥራት ጭራሽ ሚሊየነር መሆን አይችልም ግን ማለት አይደለም፡፡
ይህም ማለት በኦንላይን ላይ የሚሰሩ ሥራዎች ብዙ ዓይነት ስለሆኑ ሁሉንም በአንድ መስመር ላይ በማድረግ ለመፍረድ ያቸግራል፡፡ ስለዚህ እንደ ሥራው ዓይነትና ህጋዊነት ይወሰናል ማለት ነው፡፡ ለምሳሌ፡- እንደ ጎግል፣ አማዞን ፣ አሊባባና ፌስቡክ አይነት ካምፓኒዎች ያኔ እንደጀመሩ ሰሞን በአጭር ጊዜ ሚሊየነር መሆን የቻሉና አሁን ላይም ቢሊየነር ሆነው ከራሳቸው አልፈው ለሌሎች ግለሰቦችና ድርጅቶች የሥራ ዕድል የፈጠሩ ሲሆን የኦንላይን ሥራን በእነርሱ አይን ካየነው በርግጥም በአጭር ጊዜ ውስጥ ሚሊየነር መሆን ይቻላል ማለት እንችላለን፡፡ ካለበለዚያ ግን አንድ ሰው እነርሱ የፈጠሩትን ዕድል እንኳን መጠቀም ቢችልና የኦንላይን ሥራ ልሥራ ቢል ከዚያም ገቢ ቢኖረው እንኳን በአጭር ጊዜ ውስጥ ግን ሚሊየነር መሆን እንደማይችል እነርሱ ያዘጋጁት ውስብስብና ለመረዳት ከባድ የሆነው ሲስተማቸው እንኳን ራሱ ምስክር ነው፡፡
ሌላው ሰው መጠንቀቅ ያለበት ትልቅ ጉዳይ፡- በኦንላይን ላይ አስቀድሞ ኢንቨስት መደረግ የሚፈልጉ ሥራዎች ናቸው፡፡ እነዚህ ሥራዎች ትርፍ ያምጡ አያምጡ በማይታወቅበትና እርግጠኛ በማይኮንበት ሁኔታ ብዙ ሰዎች በተሰበካለቸው አታላይ ስብከት የተነሣ በዚህ የውሸት ሰንሰለት ተጠልፈው ይወድቃሉ፡፡ ከእነዚህም ሥራዎች መካከል ለምሳሌ፡- አንድን ምርት በኔትዎርክ መሸጥ ፣ ኢ-ሜይል ማርኬቲንግ ፣ ባይነሪ ፣ እና ሌሎችም ይገኙበታል፡፡
ስለዚህ በአጠቃላይ በመደበኛ በሚታየውና በሚዳሰሰው ሥራ አንዳንድ ሰዎች የተለያዩ ህጋዊ ስትራቴጂዎችን በመጠቀምና ብዙ በጀት በመመደብ በአጭር ጊዜ ውስጥ ሚሊየነር እንደሚሆኑ ሁሉ በኦንላይን ላይ ሥራ በመሥራት በአጭር ጊዜ ሚሊየነር መሆን የሚፈልግም ተመሳሳይ ስትራቴጁ በመጠቀምና የገንዘብ በጀት በማድረግ ዕድሉን መሞከር ይችላል ማለት ነው፡፡
በአጠቃላይ ግን ሃሳቡ ሲጨመቅ አንድ ሰው በኦንላይን ሥራ ላይ ገንዘብ ማግኘት ቢችልም በአጭር ጊዜ ግን ሚሊየነር መሆን አይችልም፡፡